Acha Profile

 

እንኳን ወደ ኢንሥኮ ድረገጽ በደኅና መጡ!

 

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአገራችንን የንግድ ሥርዓት ለአገራዊ ምጣኔ ኃብታዊ ዕድገት የተሻለ አስተዋጽዖ ማድረግ በሚችልበት ደረጃ ላይ ለማድረስ በተወሰዱ ርምጃዎች አካልነት በ2008 ዓ/ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 369/2008 እና የልማት ደርጅቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/1984 መሠረት የቀድሞዎቹን የኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ አትክልትና ፍራፍሬ ገበያ አክስዮን ማህበርና የግዢ አገልግሎት ድርጅትን በማዋሃድ የተቋቋመ ነው፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ ቀደም ሲል በተናጥል ሲካሄዱ የነበሩ የምርትና አገልግሎት ንግድ ሥራዎችን ውጤታማነትና አገራዊ ፋይዳ የሚያጎለብቱ የአሠራርና አደረጃጀት ማሻሻያዎችን በየጊዜው ተግባራዊ በማድረግ ራዕዩ አድርጎ ለተነሳው ገበያን በማረጋጋትና የውጭ ምንዛሪ ገቢን በማስገኘት በ2022 ተመራጭ የንግድ ተቋም ሆኖ የመታየት ትልም በትጋት እየሠራ ይገኛል፡፡

 

ኮርፖሬሽናችን በዋነኝነት ዘመናዊ የግብይት ሥርዓትንና የንግድ ህግን አክብሮ በመሥራት ጥራት ያላቸው የተመረጡ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችንና የፍጆታ ሸቀጦችን ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር በተወዳዳሪ ዋጋ በመግዛት ለህብረተሰቡ ማቅረብ፤ ለአርሶ አደሩና አምራቹ የገበያ ዕድል መፍጠር፤ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህልና ቅማማ ቅመም ወደ ውጪ ገበያ በመላክ የወጭ ምንዛሪ ማስገኘት እንዲሁም መንግሥታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት የውክልና ግዢ በማካሄድና በግዢ ዙሪያ የማማከርና የሥልጠና አገልግሎት በመስጠት የሀገር ውስጥ ገበያን ማረጋጋትና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲፋጠን የበኩሉን አስተዋፅኦ ማድረግ ቀዳሚ ተልዕኮዎቹ አድርጎ የሚንቀሳቀስ አገራዊ ተቋም ነው፡፡

 

ኮርፖሬሽናችን የሚያካሂዳቸው የንግድ ሥራዎች የተመጋጋቢነት ባህሪ ያላቸው ሲሆን በተለይም ለምጣኔ ኃብታዊ ሥርዓታችን መሠረት የሆነውን የግብርና ዘርፍ በዋነኝነት ለሚያንቀሳቅሱት አርሶ አደሮች ምርት የገበያ ዕድል በመፍጠር ሁለንተናዊ አቅማቸውን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስዋጽዖ አድርጓል፡፡ በሌላም በኩል የአምራች ዘርፉ አንድ አካል የሆኑት የአገር ውስጥ የአግሮ-ኢንዱስትሪና የፍጆታ ሸቀጥ አምራቾች ምርቶቻቸውን በገበያ ላይ ተወዳዳሪ በሆነ ዋጋ በመግዛት፣ የገበያ ዕድል በመፍጠር፣ የዘርፉን ዕድገትና አገራዊ ፋይዳ ለማጎልበት ሲሠራ ቆይቷል፤ እየሠራም ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝም በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ የመሠረታዊ ፍጆታ ሸቀጦችን የዋጋ ንረትና የምርት እጥረት ተከትሎ በሸማቹ ህብረተሰብ ላይ የሚፈጠረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ምርቶቹን ከአገር ውስጥና ከውጭ አምራቾች ገዝቶ ክምችት በመያዝ የገበያ ማረጋጋት ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ ለአገራችን የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ ዋነኛ የግብርና ምርት የሆነውን ቡናን ጨምሮ የተለያዩ የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ ገቢን በማስገኘት ተሸላሚ የሆነባቸው ጊዜያት ለኮርፖሬሽናችን አገራዊ አለኝታነት አንኳር ማሳያዎች ናቸው፡፡

 

ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም ኮርፖሬሽናችን በተለያዩ ጊዜያት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተጠቂ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ በማድረግ፣ የሥርዓተ-ጾታና ወጣቶች ጉዳይን በኮርፖሬሽኑ ስትራቴጂክ ሥራዎች ውስጥ በማካተት፣ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመከወንና ለሴቶች ማኅበራት ድጋፍ በማደድረግ የህብረተስብ አጋርነቱን አረጋግጧል፡፡

 

በቀጣይም ኮርፖሬሽኑ የንግድ ሥርዓታችንና በማዘመንና በምጣኔ ኃባታዊ ግስጋሴገያችን ወስጥ ማበርከት የሚችለውን አስተዋጽዖ ሁሉ በተሟላ አቅም እንዲተገብርና አሁን አገሪቱ ከደረሰችበት ዕድገት አኳያ መንግሥት እየተከተለ ካለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርህ አኳያ ኮርፖሬሽኑ በንግዱ ዘርፍ ውስጥ መጫወት የሚገባው መንግሥታዊ ሚና በአግባቡ መውጣት እንዲያስችለው የ10 ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በመንድፍ ለተግበራዊነቱ እየሠራ ይገኛል፡፡

 

ከዚኅ ጎን ለጎን ዓለማችን በደረሰችበት ሁለንተናዊ የዕድገት ሥልጣኔ ብሎም የግሎባላይዜሽን ሂደት ውስጥ የመረጃ ልውውጥ ዓይነተኛ የዕድገት መሣሪያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በተለይም በዓለም አቀፋዊ የንግድ ሥርዓት ውስጥ በገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቆየት ብሎም የተሻለ ውጤት ለማምጣት የተደራጀና በቀላሉ ተደራሽ የሆነ መረጃ መኖሩ የግድ ነው፡፡ ኢንሥኮም ይህን ከግምት በማስገባት በይዘቱና በቅርጽ በየጊዜው እየተሻሻለ የሚሄድ ድረገጽ አስገንብቶ ሥራ ላይ አውሏል፡፡ በመሆኑም ኮርፖሬሽናችን ከደንበኞቹ፣ ከሠራተኞቹ፣ ከባለድርሻዎችና ከሌሎችም አጋርና ተቋማት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በመረጃ በማጎልበትና ለመረጃ ፈላጊ አካላትም የተሟላ ተቋማዊ መረጃን በማቅረብ ረገድ ይህ ድረገጽ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት እምነቴ መሆኑን እየገለጽኩ መልካም የጉብኝት ጊዜ እንዲኖርዎ እመኛለሁ፡፡

 

አቶ አቻ ደምሴ

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ