ExcerciseBook800.jpg

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለተማሪዎች መማሪያ የሚውል ከሶስት ሚሊየን በላይ መማሪያ ደብተር ከውጭ ሃገር በማስገባት በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማሰራጨት ላይ ይገኛል፡፡

ለገበያ የቀረበው ደብተር ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ፣ በቀላሉ ውሃ የማያስገባ (water proof) ጠንካራ ሽፋን (double cover) ያለው ሲሆን ዋጋው ለአዲስ አበባ በችርቻሮ 48 ብር እና በጅምላ ደግሞ 50 ብር ሲሆን ለክልሎች መጠነኛ የትራንስፖርት ታሪፍ ተጨምሮ በመሰራጨት ላይ ይገኛል፡፡ ህብረተሰቡ ደብተሮቹን በኮርፖሬሽኑ የፍጆታ ንግድ ስራ ዘርፍ መደብሮች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ስራ ዘርፍ ማከፋፈያዎችና የእህልና ቡና ንግድ ስራ ዘርፍ ማእከላት ማግኘት ይችላል፡፡

DSC_0995_032358.JPG

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከራስ ቴአትር ጋር በመተባበር የ2016 ዘመን መለወጫን ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ሆስፒታሎች ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማንና ወላጅ እናቶች በዓሉን ምክንያት በማድረግ ስጦታ የማበርከትና የመልካም አዲስ ዓመት ምኞት መግለጫዎችን የማስተላለፍ መርኃ ግብር አካሄደ፡፡

ጳጉሜን 4 ቀን 2015 ዓ/ም በተካሄደው በዚህ የእንኳን አደረሳችሁ ጉብኝትና የስጦታ መርኃ ግብር ኮርፖሬሽኑ በ160 ሺህ ብር ወጪ የተለያዩ የታሸጉ ምግቦች፣ ፍራፍሬና የንጽህና መጠበቂያዎች በማዘጋጀት በጥሩነሽ ቤጂንግ፣ በአበበች ጎበና፣ በምኒልክ፣ በዘውዲቱ፣ በራስ ደስታ፣ በየካቲት 12 እና በጋንዲ ሆስፒታሎች በመገኘት ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን፣ እናቶችና ህጻናት ከቴአትር ቤቱ ባለሙያዎች ጋር በመሆን አበርክቷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የማኅበራዊ ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት ዓለማየሁ በመርኃ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት ኮርፖሬሽኑ እየተገበረ ከሚገኛቸው የአገር ውስጥ ገበያን የማረጋጋት፣ ለአምራቹ ገበያን የመፍጠርና የኤክስፖርት ግኝትን የማሳደግ ተልዕኮዎች በተጓዳኝ በተለያዩ የማኅበራዊ ኃላፊነት ትግበራ ላይ በመሣተፍ የህብረተሰብ አጋርነቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጎለበተ መምጣቱን አስታውሰው፤ በዚህ ዓመትም ለየት ባለ መልኩ ከራስ ቴአትር የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር በተለይ በአዲስ አበባ በሚገኙ ሆስፒታሎች ሴቶችና ህጻናት ላይ በማተኮር ለ250 ህሙማን በሰው አምስት መቶ ብር የሚሆኑ የኮርፖሬሽኑን ምርቶች በመያዝ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የማስተላለፍ፣ ታማሚዎችን የማጽናናትና ድጋፍ የማድረግ ተግባር መከናወኑን አስረድተዋል፡፡

በቀጣይም ኮርፖሬሽኑ ይህን አቅመ ደካሞችን የመርዳት ተግባሩን እያጠናከረ እንደሚሄድ ቃል የገቡት ወ/ሮ ትዕግስት፤ በዚህ ረገድ መሰል ተቋማትና የህብረተሰብ ክፍሎች “ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ” የሚለውን የሀገራችንን ብሂል ወደ ተግባር በመለወጥ በተለይ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሚታዩባቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በመለየትና አቅሙ የፈቀደውን ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 
Web.JPG
 
  
ከኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋናው መ/ቤት፣ ዘርፎችና የክልል ግብይት ማዕከላት የተውጣጡ ሠራተኞች “ነገን ዛሬ እንትከል” በሚል መሪ ቃል በአገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለውን አረንጓዴ ዐሻራ የማኖርና በአንድ ጀንበር 500 ሚሊየን ችግኝ የመትከል ዘመቻ መሠረት በማድረግ ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ/ም በቢሾፍቱና በክልል ከተሞች የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር አካሄዱ፡፡
 
“የህብረተሰብ አጋርነታችንን በአረንጓዴ አሻራችን እናጎለብታለን” በሚል መሪ ቃል የኮርፖሬሽኑ አመራርና ሠራተኞች ቢሾፍቱ በሚገኘው የአዳማ ግብይት ጣቢያ በኮርፖሬሽን ደረጃ በተካሄደው የተከላ መርኃ ግብር ላይ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ የችግኝ ተከላው ለአካባቢ ደኅንነትና ጥበቃ እንዲሁም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ረገድ ሁሉም የራሱን አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሚገባውን አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡
 
መሠል የተከላ መርኃ ግብሮችን በየዓመቱ ማካሄድ ባህል በሆነበት በኮርፖሬሽኑ ዘንድሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ 28 የኮርፖሬሽኑ የግብይት ማዕከላት በአጠቃላይ 7ሺህ 423 የአቮካዶ፣ የማንጎ፣ የፓፓዬ፣ የሎሚ፣ የሙዝ እና የቡና ችግኞች የተተከሉ ሲሆን 784 አመራርና ሠራተኞች ተሣትፈዋል፡፡
 

ተጨማሪ ምስሎችን ለማየት እዚህ ይጫኑ፡፡

 

 

 

NewYearProducts.jpg

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለመጪው የ2016 ዓ/ም አዲስ ዓመት በዓል የሚሆኑ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ለገበያ ካቀረባቸው ምርቶች መካከል የዳቦ ዱቄት (ባለ 10 እና 50 ኪ/ግ)፣ ፓልም የምግብ ዘይት (ባለ 3፣ 5 እና 20 ሊትር)፣ ፈሳሽ ዘይት፣ ሽንኩርት እና ቲማቲም ይገኙበታል፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ እነዚህን ምርቶች በስሩ በሚገኙት የፍጆታ ዕቃዎች ሽያጭ ማዕከላትና በአትክልትና ፍራፍሬ ማከፋፈያ ሱቆች በማቅረብ ላይ የሚገኝ ሲሆን ለተማሪዎች መማሪያ የሚውሉ ባለ 32፣ 50 እና 100 ቅጠል ደብተሮችን በቀጣይ ቀናት ለገበያ ያቀርባል፡፡

Customers_.Forum.jpg

 

Customers_News_Web_3.jpg

የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የደንበኞችና ባለድርሻ አካላት መድረክ ግንቦት 26 እና ሰኔ 3 ቀን 2015 ዓ/ም በሻሸመኔ እና አዳማ ከተሞች ተካሂዷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የአገልግሎት አሠጣጡን ለማሻሻል በትኩረት ከሚንቀሳቀስባቸው መስኮች አንዱ በሆነው በዚህ የደንበኞችና ባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ የህብረት ሥራ ማኅበራት፣ የምርት አቅራቢዎችና አከፋፋዮች፣ የዞንና የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኃላፊዎች፣ የንግድና ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የግል ባለኃብቶችና ከኮርፖሬሽኑ ጋር በልዩ ልዩ የግንኙነት መስኮች የሚሠሩ መንግሥታዊና መንግሥታው ያልሆኑ ተቋማት ኃላፊዎችና የኮርፖሬሽኑ የሥራ ዘርፍ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

 

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አቻ ደምሴ ኮርፖሬሽኑ በመሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች አቅርቦት የሸማቹንና ኅበረተሰብና የአምራቹን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የሚሠራና በተለያዩ የምርት ማጓጓዣና ማደራጃ አውታሮች የተደራጀ መንግሥታዊ የልማት ተቋም መሆኑን አውስተው፤ በዚህም በተመጣጣኝ ዋጋ የሚቀርቡ ምርቶችን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች አቅርቦ በማረጋጋት ሠፊ ሥራዎች መሥራቱን በውይይት መድረኮቹ አስረድተዋል፡፡

 

በከፍተኛ መጠን ምርት አምርተው ህብረተሰቡ ዘንድ መድረስ ላልቻሉ አምራች የህብረተሰብ ክፍሎችም ምርታቸውን ካሉበት ድረስ በመረከብ ምርታቸው እንዲታወቅና እጥረት ያለባቸው አካባቢዎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ መሠራቱን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

 

ለኅበረተሰቡ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በየጊዜው ማሻሻል እንደሚገባ ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ መድረኩ ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ መስኮች እየከወናቸው የሚገኙ ተግባራትን በተመለከተ ግብዓቶችን በመቀመር ለህብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትና በአገሪቱም የብልጽግና ሂደት ውስጥ ተገቢውን ሚና ለመጫወት ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

 

ኮርፖሬሽኑን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግና ተደራሽነቱን ለማሳደግ፣ በአሠራርና በአፈጻጸም የሚታዩ ክፍተቶች ካሉ ተወያየቶ በመፍታት በቅንጅታዊ አሠራር የበለጠ ውጤታማ ለመሆን እንደሚረዳ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡

 

በመድረኮቹ የኮርፖሬሽኑን የሥራ ወቅታዊ አፈጻጸም የሚያሳይ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ቀርቦ አጠቃላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በውይይቶቹ እንደ ስኳርና ዘይት ካሉ መሠረታዊ የምግብ ፍጆታ ምርቶች የአቅርቦት መጠንና ኮታ፣ ሥርጭትና ኮታ፤ በምርቶች ዋጋ፤ በአገልግሎት አሠጣጥ፣ በምርት ግብይትና አቅርቦት ላይ እንቅፋት በሆኑ አሠራሮች፤ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ በተለይም ኮርፖሬሽኑ በሚያካሂደው የገበያ ማረጋጋት ሥራ ውስጥ ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጫና እየፈጠሩ ባሉ የንግድ አካላት፣ አሠራሮችና ሰው ሠራሽ ችግሮች፤ በምርት ጥራት፣ በጸጥታ፣ በገበያ መረጃ ተደራሽነት፣ እንዲሁም ተጠናከረው መቀጠል በሚገባቸው ተግባራት ዙሪያ ሃሳቦች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

 

 

የማኅበራዊ ትስስር ገጾቻችችን በመቀላቀልና የምርትና አገልግሎት መረጃዎችን በቀላሉና በፍጥነት ያግኙ!
ድረገጽ፡- https://www.etbc-ethiopia.com
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/etbcofficial
ቴሌግራም፡- https://t.me/etbcinfo
ዜና ኢንሥኮ አንድሮይድ መተግበሪያ፡- https://t.ly/DiXR
ዩትዩብ ቻነል፡- https://www.youtube.com/@etbcinfocom4858
አስተያየትዎን በኢሜይል አድራሻችን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ያድርሱን፡፡