Harbour

 

በዓለም አቀፍም ሆነ በአገራዊ የንግድ እንቅሰቃሴ ውስጥ በተለይም ምጣኔ ኃብትን የሚያንቀሳቅሱና የንግድ ሥርዓቱ አካላትና ማኅበረሰቡ ተሣታፊ በሆኑበት የንግድ ሥራ ውስጥ የተደራጀና ሥራዎችን በቀላጠፈ አኳኋን ለማስኬድ የሚያስቸል የሎጂስቲክስ አገልግሎት ለአገልግሎት ሰጪው የጀርባ አጥንት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢንሥኮ የሚያካሄዳቸው ምርት ተኮር የሆኑ የንግድ እንቅስቃሴዎች በምርት በአገር አቀፍ ደረጃ በሚከናወኑ የምርቶች ግብይትና ዝውውር ላይ የተመረከዙ እንደመሆናቸው ለዚሁ አገልግሎት የሚውሉ ተሸከርካሪዎች መኖርና በአግባቡ ሥራ ላይ መዋል መሠረታዊ ነው፡፡ አገልግሎቱ የምርት ግዢና ሽያጭ ሥራዎችን በማቀላጠፍ ተገቢውን አገልግሎት በተገቢው ጊዜ እንዲሠጥ ያስችላል፡፡

 

ለዚሁ አገልግሎት መሳለጥም ለተሸከርካሪዎች መደበኛና የተሟላ ጥገና ማድረግ የሚያስችል የመሣሪያና የጥገና ማዕከል ያስፈልጋል፡፡ በኮርፖሬሽኑ የእህልና ቡና ማደራጃ ማዕከል የሚገኘው የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሥራ ክፍል ይህን አገለግሎት ለበርካታ ዓመታት ሲሰጥ ቆይቷል፤ እየሰጠም ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ የአገልግሎት አንድ አካል የሆነው የተሸከርካሪዎች ጥገናና እንክብካቤ አገልግሎቶች ሲሰጡባቸው የነበሩ አውታሮች ከኮርፖሬሽኑ የንግድ ሥራዎች ስፋትና አቅም ተመጣጣኝ ሳይሆኑ በመቆየታቸው ለባለሙያዎችና የሥራ አፈጻጸም ማነቆ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በተለይም ጥገናዎች የሚናወኑበት ደረጃውን የጥገና ማዕከል ባለመኖሩ የቴክኒክ ባለሙያዎች ጸሐይና ዝናብ እየተፈራረቀባቸው መሣሪዎችም ለብልሽት ተጋላጭ ሆነው አገልግሎቱ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

 

ይህን ማነቆ ለመፍታትና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ኮርፖሬሽኑ በቅርቡ በወሰደው እርምጃ ለባለሙያዎችና ለተቀላጠፈ አሠራር በሚያመች መልኩ የአዳዲስና ዘመናዊ ጥና ማዕከሎች ግንባታ ተጀምሮ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ግንባታው በአንድ ጊዜ ለ17 ተሸከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሲሆን ባለሙያዎችም በማንኘውም የአየር ሁኔታ ሥራቸውን ማከናወን የሚችሉበት ነው፡፡

Consumer products 2

 

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በፍጆታ ሸቀጦች ንግድ መስክ በአገሪቱ የንግድ ሥርዓት ውስጥ የሚስተዋሉ የተዛቡ የንግድ አሠራሮችን ለማስተካከል፣ ለዋጋ ግሽበት መንስዔ የሆኑ አሠራሮችን ለመፍታት፣ የተለያዩና በርካታ ሸቀጦችን በአንድ ሥፍራ ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ ዘመናዊ የንግድ አሠራርን ለማስፈን እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ቀደም ሲል “አለ በጅምላ” መጠሪያ ይታወቅ የነበረው የንግድ ዘርፍ ሲመሠረት የተፈጠሩና የፋይናንስ ማነቆዎችንና ውጣ ውረዶቸን በመቋቋም ተልዕኮዎቹን በተለይም የገበያ ላይ ውድድርን በብቃት አሸንፎ ገበያን ከማረጋጋትና የህብረተሰቡን የመሠረታዊ ሸቀጦቸ ፍላጎት ከማሟላት እንዲሁም ለአገር ውስጥ አምራቾች የገበያ ዕድልን ከመፍጠር አኳያ እየሠራ ይገኛል፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ በዚህ ዘርፍ ስላከናወናቸው ዓበይት ተግባራትና አገራዊ እንዲሁም በዓለመ አቀፍ ደረጃ በሁሉም ማኅበረ-ኤኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ላይ የሚገኘው የኮቪድ-19 በሽታ በግብይት ሥራ ላይ ስላስከተለው ተጽዕኖ፣ አንዲሁም በሸማቹ ኅብረተሰብ በተለይም ዝቅተኛ የኤኮኖሚ አቅም ያላቸው ላይ የተፈጠረውንና ለወደፊትም ሊፈጠር የሚችለውን የሚፈጠረውን ኤኮኖሚያዊ ጫና ከመቋቋም አኳያ ዘርፉ በምርት ክምችትና እና አቅርቦት ረገድ እያከናወ ያለውን ሥራ በዚህ ጽሑፍ እንዳስሳለን፡፡

 

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አንድ የንግድ ዘርፍ የሆነው የፍጆታ ዕቃዎች ንግድ ሥራ ዘርፍ በአለ በጅምላ ሥያሜ ሲቋቋም ምርቶችን 60 በመቶ ከውጭ በማስገባትና እና 40 በመቶውን ከአገር ውስጥ አምራቾች በመግዛት ነበር የአገሪቱን ገበያ የማረጋጋት ሥራን ሲከናውን ቆቷል፡፡ ዘርፉ በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ ኩባንያዎችን ለማበርታትና የውጭ ምንዛሬንም ለማዳን ከውጭ የሚያስገባውን ምርት መጠን በመቀነስ አብዛኛውን ምርት ከአገር ውስጥ በመግዛት ለገበያ ያቀርባል፡፡ በዚህም ከበርካታ ኩባንያዎች ጋር የገበያ ትስስርን መፈጠር ችሏል፡፡ የንግድ ዘርፉ ለሽያጭ የሚያቀርባቸው ምርቶች (ለስላሳ መጠጦች፣ የፍጆታ ሸቀጦች ፣ የታሸጉ ምግቦች፣ የቤትና የግል ንጽሕና መጠበቂያዎች፣ የጽሕፈት መሣሪያዎች፣ የምግብ ዘይትና ስኳር ምርቶችን በመንግሥት በሚወጣ የዋጋ ተመን መሠረት እንደ መሣሪያ በመሆን ለኅብረተሰቡ ያደርሳል፡፡ የምርቶችን ሚዛናዊ ሥርጭት ለመረጋገጥም አካባቢው የሚገኙ የንግድ ቢሮዎች በሚያቀርቡት መረጃ መሠረት ምርቶችን በማሠራጨት የገበያ ማረጋጋት ሥራውን በከፍተኛ ደረጃ እያከናወነ ይገኛል፡፡

 

የንግድ ዘርፉ ለሸማቹ የሚያቀርባቸው አብዛኞቹ የለስላሳ መጠጦች፣ ዱቄት፣ የታሸጉ ምግቦች፣ የንጽሕና መጠበቂያዎች፣ መቆያና ጣፋጭ ምግቦች ሙሉ በሙሉ ለማለት ለሚያስችል ደረጃ ከአገር ውስጥ አምራቾች የሚቀርቡ ናቸው፡፡

 

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውና ተጽዐኖወ ከቀን ወደ ቀን እያየለ የመጣው የኮቪድ-19 በሽታ እንደማንኘውም የኤኮኖሚ ዘርፍና የንግድ ተቋም ሁሉ በኮርፖሬሽኑ የፍጆታ ዕቃዎች ንግድ ላይ ተጽዐኖ ማድረሱ አልቀረም፡፡ ከዘርፉ እንቅስቃሴ ጋር በተየያዘ በሽታው የሠራተኞችን ሙሉ አቅም ተጠቅሞ ሥራዎቹም ማከናወን የሚችልበትን አቅም መቀነሱና በተወሰነ ደራጃመ ቢሆን ስን-ልቦናዊ ጫና ማድረሱ አልቀረም፡፡ በተለይም የዘርፉ የንግድ ሥራ ከውጭ ምርቶችን በዋነኝነት የበሽታው ሥርጭት በተስፋፋበት በጅቡቲ በኩል የሚገቡ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአሽከርካሪዎችና በሌሎችም ላይ ስጋት ወለድ ተጽዕኖ ፈጥሯል፡፡ ይሁን እንጂ ለእነዚህ ችግሮቸ ሳይበገር የተወሰኑ ሠራተኞች በፈረቃና ከቤት ሆነው መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ በማመቻቸት በዚህ ወቅት እንደ ወታደር ከፊት በመቆም ኅበረተሰቡ የምግብና ሌሎች የፍጆታ ዕቃዎችን ማግኘት እንዲችልና የተቸገሩ ሰዎችም የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተለይ በዱቄት፣ በፓልም ዘይት፣ በፓስታና ማካሮኒ አቅርቦት ረገድ ከወትሮው በተለየ የላቀ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

 

በበሽታው ምክንያት የኤኮኖሚ ተጽዕኖ ስር ለወደቁ ወገኖች በተለይም ለአረጋውያን ዕርዳታ የሚያደርጉ ድርጅቶች ከክፍለ ከተማ እና ከከተማ አስተዳደሩ ይዘው በሚመጡት መረጃ መሠረት የዱቄት፣ ፓስታ፣ ማካሮኒና ሌሎችንም ምርቶች ያለምንም ውጣ ውረድ ገዝተው እንዲያቀርቡ አስተዋጽዖ እያደረገ ይገኛል፡፡

 

የበሽታው የሥርጭት አድማስ እየሰፋ ከመሄድ አኳያ ወደፊት ሊፈጠር የሚችለውን የሸቀጥ እጥረት ከወዲሁ ለመከለከልም በተጨማሪም የንግድ ዘርፉ የሽያጭ ማዕካት በሚገኙባቸው በሁሉም አካባቢዎች ለሚገኙ አስከ 97 ሺህ የሚደርሱ የመንገሥት ሠራተኞች በወርኃዊነት የቀጥታ ግዢ እንዲፈጽሙ በማድረግ ተጽዕኖውን ለመቀነስ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፡፡ ለአብነትም ከ46 ኮንቴይነር በላይ ፈሳሽ ዘይት ከውጭ በማሰመጣት እንዲሁም በቂ የዱቄት ምርት በመያዝ በሁሉም የሽያጭ መጋዘኖች በበቂ ሁናቴ እንዲኖር በማድረግ ሊከሰት የሚችለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የተቻለ ሲሆን ከተለያዩ ክልሎች የሚመጡ ተጠቃሚዎች የሽያጭ አገልግሎት እንዲያገኑ ተደርጓል፡፡

 

ለኮርፖሬሽኑ የሚቀርብ ምርትን በተመለከተ በተለይ ከውጭ የምርት ግብዓቶችን (ጥሬ ዕቃ) አስመጥተው የሚያመርቱ ኩባንያዎች ላይ ኮቪድ-19 ችግር መፍጠሩ አልቀረም፡፡ በዚህ ረገድ ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ አማራጮችን በመውሰድ ምርት በቅድሚያ የሚያገኝበትን ዕድል በመፍጠር ከምንጊዜውም በተሻለ ሁኔታ ምርት በመጋዘን በመያዝ ለማኅበረተሰቡ ምርቶችን ተደራሽ በማድረስ ላይ ነው፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ፣ በደሴና በሻሸመኔ ቅርንጫፎች በቂ ምርት እንዲኖር ተደርጓል፡፡

 

ሠላም ለሁሉም ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መሠረት ነው፡፡ ሠላም በታጣ ቁጥር አምራችና የንግድ ተቋማት ሁሌም ስጋት ውስጥ መውደቃቸው አይቀርም፡፡ በቅርቡ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በአገሪቱ በተከሰተው ሁከት ምክንያት በአዲስ አበባና ሻሸመኔ የሚገኙ የኮርፖሬሽኑ የፍጆታ ዕቃ መደብርና መጋዘኖች በመዘጋታቸው ለተወሰኑ ቀናት ለኅብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ሳይቻል ቀርቷል፡፡ በሌላም በኩል የተስተጓገለውን የሽያጭ አገልግሎት የደሴ፣ የባህር ዳርና የአዋሳ የሽያጭ መደብሮች ተጨማሪ አቅም ፈጥረው እንዲሠሩ በማድረግ ለማካካስና ችግሩን ለመቋቋም ጥረት ተደርጓል፡፡

 

ኢንሥኮ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት የንግድ ሥራውን አፈጻጸምና ፋይዳ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ዕቅድ ነድፎ መንቀሳቀስ ከጀመረ ሰነበብቷል፡፡ በተለይም ለኦፕሬሽን ሥራዎች ልቀት ቀዳሚ ትኩረት በመስጠት በግዥና ሽያጩ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ለአምራቹ ገበያ የመፍጠር ዕድል እና የሸማች ገበያን የማረጋጋት ሚና በአግባቡ ለመወጣት እየሠራ ይገኛል፡፡ በፍጆታ ሸቀጦች ግብይት እንቅስቃሴ ትኩረት ከተሰጣቸው ሥራዎች አንዱ የሽያጭ መደብሮችን ቁጥር ከፍ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ከክልሎች ጋር ተቢውን ተግባቦት በማካሄድ በየዓመቱ ቢያንስ ሁለት ተጨማሪ የሽያጭ መጋዘንና መደብሮችን በመክፈት ለህብረተሰቡ በተሻለ ተደራሽ ለመሆን ታስቧል፡፡ በጅማ፣ አዳማ፣ መቀሌ፣ ጎንደርና ወልቂጤ ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ ሥራዎች መጀመራቸውም ታውቋል፡፡

 

የአገር ውስጥ አምራቾች ጋር በተሻለ ቅርበት በመሥራትና የአገር ውስጥ ምርትን በማበረታታት የኅብረተሰቡን ፍላጎት ያገናዘበ አግልገሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ተገባራት ም የስትራቴጂክ ዕወቅዱ አካላት ናቸው፡፡ ይህም ተጨማሪ የሥራ ዕድልን፣ አገልግሎትንና ትርፍን የሚያስገኝ በመሆኑ የኮርፖሬሽኑን አቅም የማጠናከር አቅም እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

 

ከውጭና ከአገር ውስጥ አምራቾ ጋር የተጠናከረ ግንኙነት በማረግ በቂና አስተማማኝ የምርት አቅርቦት እንዲኖር የማድረግ፣ እንደ ዲመሬጅ ያሉ አላስፈላጊ ወጪዎችን መቀነስ እንዲሁም መጠነ ሰፊ ማዕካለዊ መጋዘን በማስገንባት በቂ ስቶክ ለመያዝና በጥቅሉ የገበያ ላይ ተወዳዳሪነትንና ትርፋማነትን ለማሳደግ ተወጥኗል፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ በዚህ የንግድ ዘርፍ ቶሎ ቶሉ በሚሸጡ የፍጆታ ሸቀጦችን ግብይት ላይ የተሠማራ ከመሆኑ አኳያ ሁሉንም የኮርፖሬሽን ዘርፎች ይዞ መውጣት የሚችልበት እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ ለዚህ ማነቆ የሆኑ በተለይም ከሂሳብ መዝጋትና ተገቢ ያልሆኑ ዕዳዎችን ከማሠረዝ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረቶች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከስትራቴጂያዊ ሥራዎች በተጓዳኝም ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ  ለመደበኛ ሥራዎች ሰፊ ትኩረት በመስጠትና በጠነከረ አቅም በመሥራት ወደ ትርፋማነት ለመምጣት እየተሠራ የሚገኝ ሲሆን፤ የኮርፖሬሽኑ አዲስ አመራር ከዕዳ ክፍያ ጋር ለተያያዙ ማነቆዎች እልባትን በማስገኘት ጠንካራና ለሌሎች ተጓዳኝ የኮርፖሬሽኑ ሥራዎች ጭምር አቅምን ሊፈጠሩ የሚችሉ ሥራዎችን ለመከወን እየሠራ ይገኛል፡፡

Cement

 

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአገራችን በግንባታው ዘርፍ ማነቆ ሆኖ የሚገኘውን የሲሚንቶ ዋጋ ንረትና የምርት እጥረት ለማረጋጋት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ምርቱን እንደዲያከፋፍሉ ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ/ም በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በተደረሰው ውሳኔ መሠረት ምርቱን ከአገር ውስጥ አምራቾች በመግዛት በኮንስትራክሽን ሥራ ለተሠማሩ አካላት ማከፋፈል ጀምሯል፡፡

 

ኮርፖሬሽኑ የሲሚንቶ ምርትን በቀጥታ ከአምራች ፋብሪካዎች በተለይም በዋነኝነት ከዳንጎቴ፣ ደርባና ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በመግዛት ለአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ ለጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ለአዲስ አበባ አስተዳደር ለሚገኙ የመንግሥት ፕሮጀክቶች፣ ለክፍለ ከተሞችና በግንባታው ለተሠማሩ ሌሎች አካላት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡

 

በአገራችን እየተከሰተ ባለው የሲሚንቶ ዋጋ ንረት ምክንያት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዳ እንደሚገኝና ይህንን ለማስተካከል በንግድና ኢንዱስትረ ሚኒስቴርና በሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶች መካከል ውይይቶች ሲደረጉ ቢቀይም ችግሩ ሊፈታ ካለመቻሉ በተጨማሪ በአንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የሲሚንቶ ምርት እጥረት እየተከሰተ መሆኑን ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጀ ያመለክታል፡፡

 

በመሆኑም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከአምራች ፋብሪካዎች፣ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሲሚንቶ ምርትን በቀጥታ ከፋብሪካዎች በመግዛት እንዲያከፋፍሉ፤ አምራች ፋብሪካዎችም የሲሚንቶ ምርታቸውን በቀጥታ ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች እንዲሸጡ በወሰነው መሠረት ነው ኮርፖሬሽኑ የማከፋፈል ሥራውን እየከወነ የሚገኘው፡፡

 

እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2012 ድረስ ባለው ጊዜ ከ90 ሺህ በላይ ኩንታል ሲሚንቶ ለምርት ፈላጊዎች መከፋፈሉን ከሽያጭ ክፍሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

 

Tree Planting 2012 EC s

በክረምት ወራት ችግኞችን በመትከል የተራቆተውን የአገራችንን የደን ይዞታ የመመለሱ ተግባር ላለፉት በርካታ ዓመታት በአገራችን ሲተገበር መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ ይሁን እንጂ ከጊዜ ወደጊዜ እየሰፋ በመጣው ዓለም አቀፋዊ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖና የበርሃማነት መስፋፋት ምክንያት ትገበራው የተፈለገውን ውጤት ሳያመጣ ቆይቷል፡፡ ይህን ከግንዛቤ በማስገባት መንግሥት በተለይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ አገራዊውን የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በጎለበተና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባተፈ መልኩ “የዜጎች የአረንጓዴ አሻራ ቀን እናሳርፍ፤ በአንድ ጀንበር 200 ሚሊየን ችግኝ እንትከል!” በሚል መርህ በአገር አቀፍ ደረጃ 4 ቢሊየን ችግኞች እንዲተከሉ ተደርጓል፡፡

 

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንም ሁሉንም ሠራተኞቹን በማስተባበር በድምሩ 12 ሺህ ያህል ችግኞች በመትከልና በመንከባከብ ለአገራዊ ግቡ መሣካት የራሱን አስተዋጽዖ ማድረጉና የታሪክ አሻራ ባለቤት መሆኑ አይዘነጋም፡፡ ዘንድሮም “5 ቢሊየን ዛፎች ለአረንጓዴ ኢትዮጵያ፡ አረንጓዴ አሻራችንን ማሳረፋችንን እንቀጥላለን” በሚል መርህ እየተካሄደ በሚገኘው የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር አካልነት ሐምሌ 4 ቀን 2012 በሁሉም የኮርፖሬሽኑ ማዕከላት ቡድን በተደራጁ ሠራተኞቹ አማካኝነት የችግኝ ተከላ አካሂዷል፡፡

 

መርኃ ግብሩ የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በሎጂስቲክስና የቴክኒክ አገልግሎት ቅጥር ግቢ የተጀመረ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባሉ የኮርፖሬሽኑ ግቢዎች ማለትም በፍጆታ ዕቃዎች ንግድ ሥራ ዘርፍ ዋና  መ/ቤትና መገናኛ ቅርንጫፎች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ወና መ/ቤት፣ በአቃቂ፣ በእህልና ቡና ንግድ ዘርፍ የቡና ማደረጃና ማከማቻ ማዕከል፣ በአደይ አበባ ግቢና በአዲስ አበባ ዙሪያ ግብይት ማዕከል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ፣ አካባቢ ጥበቃ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጾ ያላቸውንና ለውበት የሚያገለግሉ 1500 ያህል ችግኞች ከ450 በላይ ሠራተኞችን በማሳተፍ ተከላው ተካሂዷል፡፡ በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ ቀሪዎቹ የኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ መ/ቤቶች 10 ሺህ ችግኞችን የማስተከል ሥራዎች ከወዲሁ ተጀምረዋል፡፡

 

በቀዳሚው ዓመት የተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በሠራተኛው ዘንድ ጥሩ መነሳሳትንና እንደ አገር ለአረንጓዴ ልማት ያለውን ጠቀሜታን በተመለከተ ግንዛቤን የፈጠረ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህ ዓመትም ከችግኝ ተከላ በኋላ በሚዘጋጀው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም የመንከባከብ ሥራ እንደሚከናወንና በዚህም የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጁነት መኖሩን ተገልጧል፡፡

 

ለአትክልትና ፍራፍሬ ዛፎች ልዩ ትኩረት በተሰጠበት በዘንድሮው የተከላ ፕሮግራም ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ብቻ 300 የአቮካዶ፣ 350 የማንጎ፣ 210 የዘይቱንና 220 የሎሚ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን 710 የጃካራንዳና 210 የሚሊያ ዛፍ ችግኞች ተከላም ተከናውኗል፡፡ የእንክብካቤ ሥራዎችም ለአፈጻጸም በሚያመች መልኩ ሠራተኛውን በየሥራ ክፍሉ በቡድን ተከፋፍሎ የሚያከናውኑበት አሠራር መመቻቸቱን ታውቋል፡፡

 

 

 

 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ አባላት የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሥራ እንቀስቃሴ የሚገመግም ጉብኝት በኮርፖሬሽኑ ዋና መሥሪያ ቤትና በዘርፍ መ/ቤቶች አካሂደዋል፡፡

አባላቱ በቆይታቸው አራቱምን የኮርፖሬሽኑን የሥራ ዘርፎች ወቅታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያደመጡ ሲሆን በኮርፖሽኑ የፍጆታ ዕቃዎች የንግድ ሥራ ዘርፍ መ/ቤት፣ በሎጂስቲክስ አገልግሎትና በእህልና ቡና የንግድ ዘርፍ የቡና ማደራጃ ማዕከል በመገኘት የሥራ እንቅስቃሴ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

በጉብኝቱ ላይ የኮርፖሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች በየዘርፉ እየተከናወኑ ያሉና አገራዊ ጠቀሜታቸው የጎላ ተግባራትን ለአባላቱ ያብራሩ ሲሆን በአንጻሩ የአፈጻጸም ክፍተት የሚታይባቸውንና መንግሥታዊ ድጋፍን የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት ለኮሚቴው አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም የቋሚ ኮሚቴው አባላት ከኮርፖሬሽኑ የሠራተኛ ማኅበር ተወካዮች ጋር በመገናኘት መሻሻል በሚገባቸው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ ኮርፖሬሽኑ የዋና መ/ቤትና የዘርፍ የሥራ ኃላፊዎች ጋር አጠቃላይ ውይይት አበረታች ተግባራትን ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማሳሰብ፣ ኮርፖሬሽኑ ሊያሻሽል ይገባዋል ባሏቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫዎች በማስቀመጥና በኮርፖሬሽኑ የሥራ አፈጻጸም ላይ ተግዳሮት የሚፈጥሩ ጉዳዮቸን ለመፍታት በሚያስችሉ አካሄዶች ላይ የጋራ ግንዛቤን በመውሰድ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠሩ አስረድተዋል፡፡