የኢትዮጵያ የንግድ ሥ ራዎች ኮርፖሬሽን በ2010 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና በ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ከደንበኞችና ባለድርሻ አካላት ጋር ህዳር 4 ቀን 2011 ዓ/ም በግሎባል ሆቴል ውይይት አካሂዷል፡፡

በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት አገልግሎት ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታሪኩ በራሱ የምክክር መድረኩን ሲከፍቱ የኢትዮጵያ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን በ2010 በጀት ዓመት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ገበያ 7.21 ሚሊዮን ኩንታል እህል፣ ቡና፣ አትክልትና ፍራፍሬ እና የፍጆታ ዕቃዎች ለመሸጥ አቅዶ 7.77 ሚሊዮን ኩንታል ያከናወነ መሆኑን በ2011 በጀት ዓመት 8.72 ሚሊዮን ኩንታል ለመሸጥ ማቀዱን ገልጸዋል፡፡

የደንበኞች አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በበጀት ዓመቱ አሰራሩን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችን የመተግበርና የሰራተኞቹን አቅም የሚያጎለብቱ በካይዘን አመራር ፍልስፍና ጽንሰ ሃሳብ፣ በአለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት አዘጋገብ / IFRS /፣ በምርት ጥራትና ክምችት አያያዝ እንዲሁም በውጭ ንግድ ሥርዓት ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎች ለኮርፖሬሽኑ አመራርና ፈጻሚዎች መስጠቱን ም/ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል፡፡

ለገበያ ማረጋጊያ በኮርፖሬሽኑ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራት ማረጋገጥ፣ ምርቱ መቼ፣ የት እና በማን እንደተገዛ የሚገልፅ ግልጽ አሠራር ተግባራዊ ማድረግ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን አቅርቦት ሳይቆራረጥ ለተጠቃሚው ለማቅረብ የኮንትራት ፋርሚንግን አሠራርን ተግባራዊ ማድረግ፣ የፍጆታ ዕቃዎች ተደራሽነትን ለማሳደግም አቅርቦትና ፍላጎትን ማጣጣም የሀገር ውስጥና አለም አቀፍ ግዥዎች የመፈጸም አቅምን ማሳደግ በበጀት ዓመቱ ትኩረት የተሰጣቸው ሥራዎች እንደሆኑ በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ደንበኞቹና ባለድርሻ አካላት በሚጠብቁበት ደረጃ አገልግሎቱን ለመስጠት እና ባቀደው ዕቅድ ልክ አፈጻጸሙን ለማሳካት በሀገር ውስጥ በሚፈለገው መጠንና ዋጋ የእህል ምርት ገበያው ላይ አለመገኘት፣ በመንግሥት ድጎማ ለገበያ ማረጋጊያ ከውጭ ሀገር የሚገዛውና በኮርፖሬሽኑ የሚሰራጨው የውጭ ስንዴ ግዥ ጨረታ መስተጓጎል ለገበያ ማረጋጊያ ከውጭ ለሚገዙ የፍጆታ ሸቀጥ ምርቶችም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ፍላጎትና አቅርቦቱ አለመመጣጠን፣ ኮርፖሬሽኑ ለውጭ ገበያ የሚቀርባቸው የቡና፣ የቅባት እህልና ጥራጥሬ ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ካለው የገበያ ዋጋ መብለጥና የምርቶቹ ዋጋ መዋዥቅ ዋነኛ ችግሮች መሆናቸው በውይይቱ ወቅት ተብራርቷል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የአገር ውስጥና የውጭ ስንዴ ግዥ ጥራት ኢንዱስትሪውን ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን እንዲሁም እያጋጠመ ላለው የፍጆታ እቃዎች እጥረት ኮርፖሬሽኑ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንዲፈለግ ጠይቀዋል፡፡ በመድረኩ ላይ እህል አቅራቢ የሆኑ አርሶ አደሮች፣ ህብረት ሥራ ማህበራት፣ ለገበያ ማረጋጊያ ከኮርፖሬሽኑ ስንዴ የሚገዙ የዱቄት ፋብሪካ ባለንብረቶች፣ ከኮርፖሬሽኑ በጋራ የሚሠሩ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች እና ማህበራዊ ተቋማት ተሣትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን በጥሬ ገንዘብና በዓይነት በድምሩ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ለመቄዶኒያ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን ማዕከል አደረገ፡፡ የኮርፖሬሽኑ አመራርና ሠራተኞች የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ታህሳስ 24 ቀን 2011 ዓ/ም አዲስ አበባ አያት የሚገኘው ማዕከል በመገኘት አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማንን ጎብኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለመቄዶኒያ አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማን ማዕከል ያደረገው ድጋፍ በጥሬ ገንዘብ ብር 355,873 ሲሆን ቀሪው በዓይነት በድምሩ አንድ ሚሊዮን ብር የሚገመት ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በዓይነት ለማዕከሉ ድጋፍ ያደረጋቸው ምርቶች 100 ኩንታል ነጭ ጤፍ፣ 20 ኩንታል ሽንብራ፣ 40 ኩንታል ስኳር፣ አንድ ካርቶን (368 ፍሬ) ሻይ ቅጠል፣ 7.5 ኩንታል ማካሮኒ፣ 200 ሊትር ዘይት፣ 236 ሊትር ላርጎ ፈሳሽ ሳሙና፣ 18 ባለሁለት ሊትር ፈሳሽ ሳሙና፣ 100 ፍሬ አጃክስ ሳሙና፣ 20 ኩንታል ሙዝ፣ 10 ኩንታል ብርቱካን፣ 240 ጣሳ ማርማላት፣ 995 ጣሳ ቲማቲም ድልህ እና ግምታቸው አስር ሺህ ብር የሆነ ልባሽ አልባሳት ናቸው፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መንግሥቱ ከበደ እና የሠራተኛ ማህበር ተወካዮች ድጋፉን ለማዕከሉ መስራች ክቡር ዶክተር ቢኒያም በለጠ ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት አስረክበዋል፡፡ በቀጣይ ማዕከሉን በዘላቂነት ለመደገፍ የኮርፖሬሽኑ አመራርና ሠራተኞች ዝግጁ መሆናቸውን ድጋፉ በተደረገበት ወቅት የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መንግሥቱ ከበደ ገልፀዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የህብረተሰቡን የፍጆታ ዕቃዎችና የምግብ ምርቶች ፍላጎት ለማሟላትና የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት የተቋቋመ እንደመሆኑ መጠን ለማዕከሉ የሚያስፈልጉ የእህል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የፍጆታ ዕቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ዘላቂ ድጋፍ ለማድረግ እንደተዘጋጀም ተናግረዋል፡፡

ሀገሪቱ ፖለቲካ ስልጣን የበላይ የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤትና በቅርንጫፍ የንግድ ግብይት ማእከላትበአካል በመገኘት የኮርፖሬሽኑን አጠቃላይ የንግድእንቅስቃሴ ገምግመዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በአቶ መንግስቱ ከበደ ስለ ኮርፖሬሽኑ አመሠራረት፣ አደረጃጀት እና አሠራር እንዲሁም ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ያከናወናቸውን ዋና ዋና ተግባራት በተመለከተ ሰፊ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን አያይዘውም በአሁኑ ጊዜ ኮርፖሬሽኑን በአሠራርና በአገልግሎት አሰጥጥ ያጋጡሙትን መሠረታዊ ችግሮች አስመልክቶ በቀድሞው አለ በጅምላ ላይ የነበሩ የአሰራር ችግሮች እንዲሁም የእህል መጋዘኖችን ለማስፋፋት የመሬት ጥያቄ በተመለከተ የአዳማ መጋዘን ርክክብ መጓተት እና የከተማ አስተዳደሩ ምላሽ መዘግየት ኮርፖሬሽኑ ውጤታማና ትርፋማ እንዳይሆን ዋና ችግሮች እንደሆኑ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በቅድሚያ አስረድተዋል፡፡

የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እህልና ቡና፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የፍጆታ ዕቃዎች ንግድ ሥራዎች እንዲሁም በግዥና ማማከር የአገልግሎት ዘርፎችን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡ የኮርፖሬሽኑን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትና የንግድ ትስስር ሥራዎችን በተመለከተ የፎቶ አውደ ርዕይ በፎቶ መስኮት፣ የተለያዩ የሥራ ክፍሎችን እንቅስቃሴና የውጤት ተኮር አሠራር አተገባበርና ያስገኘው ውጤት በተመለከተ ከኃላፊዎችና ባለሙያዎች ገለጻ የተሰጣቸው ሲሆን፤ መስተካከል በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ አስተያየት በመስጠት ክፍተቶች እንዲታረሙ አሳስበዋል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ኮርፖሬሽኑ በግዢና ማማከር አገልግሎት ዘርፍ የሚሠራቸውን ሥራዎች አስመልክቶ በአዲስ አበባና በእህልና ቡናና በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ሥራ ለገበያ ማረጋጊያና ለወጭ ንግድ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን ማቀነባበሪያ ማደራጃና ማከማቻ ማዕከላትን የፍጆታ ዕቃዎች ንግድ ሥራ ቃሊቲ መደብር እንዲሁም የአዳማ ቅርንጫፍ የግብይት ማዕከላትን ጎብኝተዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱም ኮርፖሬሽኑ በአዳማ ቅርንጫፍ የግብይት ማዕከል የሀገር ውስጥ ገበያን ለማረጋጋት ለሀገር ውስጥ ገበያ ማረጋጊያ የሚደራጁ ምግብ ስብሎችንና ለዓለም ገበያ የሚቀርበው የቦሎቄ ምርት ጥራትን ለማስጠበቅየሚከናወኑ የእህል ጥራት ማስጠበቂያ መሣሪዎች አጠቃቀምን በመስክ ምልከታው ጎብኝተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ዘውዱ የኮርፖሬሽኑን የዕቅድ አፈጻጸም በመስክ ጉብኝት ለማረጋገጥ ባስቀመጠው መመዘኛ (መገምገሚያ) መስፈርት መሠረት የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2009 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን መሠረት በማድረግ በሰጠው የዕቅድ ግምገማ ግብረመልስ መሠረት ኮርፖሬሽኑ ከሚጠበቀው በላይ ውጤታማ አፈጻጸም በማስመዝገቡ ከፍተኛ እርካታ እንዳገኙ ገልጸው ቋሚ ኮሚቴው የያዘውን ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ማሳካቱን ተናግረዋል፡፡

ሌሎች የቋሚ ኮሚቴ አባላትም በተመሳሳይ ዕቅዱና አፈጻጸሙ የተጣጣመ እንደሆነ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ከበደ የኮርፖሬሽኑ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ የፍጆታ ዕቃዎች ንግድ ሥራ የአዳማ ቅርንጫፍ ለመክፈት ያጋጠሙ አስተዳደራዊ ችግሮች እንዲሁም የእህል መጋዘኖችን ለማስፋፋት የመሬት ጥያቄና የከተማ አስተዳደር ምላሽ መዘግየትና የመሳሰሉት መሠረታዊ ችግሮችን በመቅረፍ በኩል በተለይ በውጭ ንግዱ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደሩ ያሉ ችግሮችን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የአዳማ ከተማ አስተዳደር በመተባበር ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወጪ ንግድ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስገኙ ላኪዎች፣ ገንዘብ አስተላላፊዎችና አገልግሎት ሰጪ ደንበኞቹን ታህሳስ 11 ቀን 2011 ዓ.ም በሂልተን ሆቴል ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ የንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን በ2010 በጀት ዓመት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የፕላቲኒየም ተሸላሚ ሆኗል፡፡ ኮርፖሬሽኑ የቡና፣ ቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬና የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ 26.776 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር አስገኝቷል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በተመሳሳይ ባስገኘው የውጭ ምንዛሪ መጠን ተሸላሚ መሆኑ ይታወቃል፡፡